Saturday, March 12, 2011

ቼርኖቤል የኒውክለር ማብለያ ጣቢያ ድንገተኛ አደጋ።


ቼርኖቤል በቀድሞ ሶቭየት ህብረት አካል የነበረች በዮክሬን ግዛት ውስጥ የምትገኝ የሃይል ማመንጫ ጣቢያ ናት። ከፕሪፒያት ከተማ በ3ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የተተከለው ቼርኖቤል ኒውክለርን በመጠቀም የኤለክትሪክ ሃይል የሚያመነጭ ጣቢያ ነው። አርብ ሚያዝያ 18,1978 አ.ም. እኩለ ሌሊት በቼርኖቤል ኒውክለር ማብለያ ጣቢያ ውስጥ በደረሰው ፍንዳታ የድንገተኛ አደጋ አገልግሎት ሰጪዎችን እና ተመራማሪዎችን ጨምሮ ለአራት ሺህ ሰዎች ህይወት መጥፊያ ሲሆን ከሶስት መቶ ሰላሳ ስድስት ሺህ ሰዎች በላይ ለመፈናቀል ምክንያት ሆኗል። የፍንዳታው ውጤት ሶቭየት ህብረት፤ ምስራቅ ፤ምእራብ እና ሰሜን አውሮፓን አጥቅቷል። በይበልጥ የችግሩ ሰለባ የሆኑት ዮክሬን ቤላሩስ ራሺያ ነዋሪዎች ነበሩ። የደረሰውን አደጋ በቁጥጥር ስር ለማዋል ባሁኑ ገንዘባችን ሲሰላ አንድ ትሪሊዮን አንድ መቶ ሃያ አምስት ሚሊዮን ብር ፈጅቶአል።

በደረሰው ፍንዳታ የተመረዘውን ቦታ በፍጹም ማጽዳት የማይቻል ሲሆን። ጣቢያው የተተከለበት ህንጻ ዙርያውን መጠኑ ተወዳዳሪ በማይገኝለት ወፍራም ግንብ ታሽጓል። ነገር ግን የታሸገበት ግንብ ለሰላሳ አመት ድረስ ያህል እንዲያገለግል ሆኖ ነው የተሰራው። አሁን አደጋው ከደረሰ ከሃያ አመት በላይ ሆኖታል። በኒውክለር ጨረር የተመረዙ ሰዎች እና የሚወልዱት ልጆቻቸው የአደጋው ሰለባ መሆናቸውን ግን እስካሁን አላቋረጡም።

“…ቼርኖቤል የኒውክለር ሃይል በሰዎች እጅ ሲገባ እንዴት እንደሆነ ሃይሉን አሳይቶናል። እኛ ያሉንን ኤስ ኤስ 18 ሚሳኤሎቻችንን ስናሰላቸው እያንዳንዱ ከመቶ ቼርኖቤል በላይ ሃይል ያላቸው ናቸው። ኤስ ኤስ 18ትን አሜሪካውያን ከምንም በላይ የሚፈሩት የጦር ሚሳኤል ነው። እኛ ሁለት ሺህ ሰባት መቶ የሚሆኑ አሉን። እነዚህ ሚሳኤሎች እኛ ለአሜሪውያኑ ብለን የሰራናቸው ናቸው። ሁለት ሺህ ሰባት መቶ አስቡት ሊያመጡት የሚችሉት ጥፋት።…”

-----ሚካኤል ጎርቫቾቭ የቀድሞ የሶቪየት ህብረት ፕሬዘዳንት እና የሶቪት ህብረት ኮሚኒስት ፓርቲ ዋና ጸሃፊ