"ቋንቋችንን እንጠብቅ"
በስመአብ ወወልድ በመንፈስ ቅዱስ አሃዱ አምላክ አሜን። በእግዚአብሄር ፈቃድ ይህችን ለማለት ወደድኩኝ ። ማንነት በሰብናችን ላይ የሚጫወተው ሚና የትዬለሌ ነው ። ስለ እኛነታችን ማንነታችን አፍ አውጥቶ ይናገራል ማንነት ለራሳችን ካለን አመለካከት በዋናነት ይመነጫል ስለ ራሳችን ያለን ያለን አመለካከት ደግሞ በከፍተኛነት ስለራሳችን ካለን ግንዛቤ እና ዕውቀት ይመነጫል። ስለዚህ ማንነት ማለት አንድ ሰው ከመጣበት ወይንም ከሚወለድበት ሀገር ፣ የዘር ሀረግ፣ ቤተሰብ ፣ ህብረተሰብ ፣ የሚወርሰውን እንደ ሐይማኖት ፣ሀገር ፣ባህል እና ቋንቋዎች ላሉ እሴቶች ያለው አመለካከት የግለሰቡን ማንነት ይሰጡታል። ይንን አጠር ያለጽሁፍ ለማቅረብ መነሻ የሆነኝ እ.ኤ.አ 2004 በአቶ አማረ አፈለ የተጻፈው ኢትዩጵያ የሰው ዘር የተገኘባት የእምነትና የሥልጣኔ ምንጭ ናት የሚለው መጽሃፋቸው ነው።
እኔ ስለራሴ ያለኝ ግንዛቤ፣ ዕውቀት እና መረጃ የተሳሳተ እና የትምታታ ከሆነ ለራሴ ያለኝ እመለካከትም እንደዚሁ የተዛባ እና ዝቅያለ ይሆናል።እዚህ ላይ አንባቢዎቼ እንዲረዱልኝ የምፈልገው ነገር ስለራሳችን ስል በግል ሳይሆን በጋራ ስለምንጋራችው እሴቶች ማለቴ ነው።ለምሳሌ ሃይማኖት፣ ባህልን፣ ቋንቋን እና ሀገርን በዋናነት የሚመለከት መሆኑን እሳቤ ውስጥ እንዲገባልኝ አሳስባለሁ። አንድ ሰው ስለ ስለሃማኖቱ፣ ቋንቋው፣ ባህሉ እና ሃገሩ ያለው አመለካከት፣ግንዛቤ፣ መረጃ እና እውቀት የተሳሳተ እና የተንሸዋረረ ክሆነ በግለሰብነት ደረጃ ስለራሱ ያለው አስተሳሰብ እንደዛው የተምታታበት እና የተወላገደበት ይሆናል። ይባስ ብሎም በነጋ በጠባ የሚሸማቀቅበት ይሆናል። በዚህ ብቻ አያበቃም ማንነት የሌለው ባይተዋርነት ስሜት በተደጋጋሚ ይሰማዋል ይህ ደግሞ አደገኛ የሚሆንበት ጊዜ አለ ። ይህም ሐይማኖት፣ ቋንቋ ፣ባህል እንደ አሮጌና እንዳለፈባቸው በመቁጠር የራሳቸን ያልሆኑ ሀይማኖቶች፣ ቋንቋዎች፣ ባህሎች ላይ የሙጥኝ እንድንል ያደርገናል ።
በዚህ ብቻ ሳያበቃ በሃይማኖታችው፣ በባህላችው፣ ቋንቋቸው ላይ የሚቃጣውን ንቀት፣ጥቃት፣ የሃሰት ወሬ፣ቧልት እና ውርደት በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ግብረአበር በመሆን የድጊቱ ተሳታፊ ሲሆኑ ይስተዋላል። በርግጥ አንድ ሰው ማንነት አልባ መሆን ጮቤ የሚያስረግጣችው አካሎች እንዳሉ የማይታበል ሃቅ ነው ።በተለይ አሁን ባለንበት ዘመን አለም አንድ መንደር በሆነችበት (ግሎባይላዜሽን) ሐይማኖት ባህል እና ቋንቋ እንደ ሸቀጥ በገንዘብ ሲቸበቸቡ እና ሲራገፉ ስናይ ይህ ማንነቱ ግራ የተጋባበት እና የተምታታበት የሰለጠነ መስሎም ስለሚሰማው ሐይማኖት፣ባህል፣ ቋንቋ እንደሌለው ብሩን አውጥቶ ሲሸምት መመልከት የሚፈጥረው ስሜት በደም ተቀላቅሎ አንጀት ያማስላል ።
አበው ነገር በምሳሌ ጥጅ በብርሌ እንዲሉ ከኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያናችን ጋር በተገናኘ አንድ ነገር ልበል ይህውም የቋንቋዎች አባት የሆነውን ግዕዝን ይመለከታል ግዕዝ ረጅም ጊዜን ያስቆጠረ እድሜ አለው እንደውም ግዕዝ ከእግዚአብሄር በቀጥታ የተሰጠን ቋንቋ መሆኑን እንናገራልን ።ግእዝ የእለት ተለት መነጋሪያነቱን እያጣ እና ተናጋሪዎቹም እያነሱ በመሄዳቸው በቤተክርስትያን ብቻ ተወስኖ ይገኛል።
ኢትዩጵያዊው በማንነቱን ፍለጋ በተባለ መጽሃፍ ገጽ 298 "ግእዝ ማለት መጀመሪያና መነሻ ራሱን የቻለና ነጻ ማለት ነው። በዕብራውያን ዕብራይስጥ ፣በአረብ አረቢኛ፣ በእንግሊዝ እንግሊዘኛ ፣እንደሚባለው ባገር ወይም በነገድ ወይም በተናጋሪው ህዝብ ሳይህን በራሱ የሚጠራ ፊደልና ሥርአቱ ራሱን ችሎና ተሟልቶ የተሰናዳ ቋንቋ ስለሆነ ግእዝ ተባለ። ይህ የቃሉ ትርጉም ግዕዝ የአዳም እና ሄዋን ቋንቋ ነበር" ሲሉ ጽፈዋል።
ግእዝ የአዳም እና የሄዋን እርስ በርሳቸው እና ከእግዚያብሔር የሚነጋሩበት ቋንቋ ነበር ይላል። ይህ ማለት እግዚአብሄር ከገነት ጀምሮ አዳም እና ሄዋንን ሲያናግርበት እንደቆየ ያሳየናል። ኦሪት ዘፍጥረት ምራፍ 11 ቁጥር 1 "ምድር ሁሉ በአንድ ቋንቋ ነበርች" ይላል። ሌላው ግእዝ ክእግዚአብሄር በቀጥታ የተሰጠን ቋንቋ ለመሆኑ ስለ መሆኑ አቶ አማረ አፈለ "ከታሪክ መጽሃፎች እንደምንረዳው የአዳም ቋንቋ ግእዝ ነበር የቀደሙ ምሁራን አብዛኛዎቹ የሚሉት የኢትዮጵያዊ ፊደል ነው" ሲሉ ጠቅሰዋል ። ፈለግ መጽሄት ጥቅምት 1985 ዓ.ም. ገጽ 39 "የኢትዩጵያ ፊደል ለምዕራቡ አለም መሰረት መሆኑ ተደረሰበት" ሲል ጽፏል። ታዲያ ይህ ሁሉ የሚያሳየው አሁን የምንጠቀምበት ፊደላችን ገዝተነው ወይም ከቀኝ ገዢዎች እንድንጠቀምበት የተሰጠን ሳይሆን ከፈጣሪያችን ከእግዚያብሔር የወረደልን ነው።
ነገር ግን ማንነታችንን አሳጥተው ትውልዳችንን በራሱ የማይተማመን ለሐሃይማኖቱን እና ለቤተክርስቲያኑ በእኔነት እና ተቆርቋሪነት ስሜት ይማይሰማው ትውልድ እንዲፈጠር አበክርው የሚሰሩ የውጭ መናፍቃን እንዳሉ በግልጽ እያየነው ነው። ይህ ብቻ ሳያንስ የነሱ የገደል ማሚቶዎች የሆኑት የውስጥ መናፍቃን የእጅ አዙር ቀኝ ገዢዎች መሳሪያ በመሆን እነሱ የሚሏቸውን እንደ በቀቀን ሲያስተጋቡ ይስተዋላል። ግእዝ ከነፊደሉ አዳም እና ሔዋን ተስጥቶአችው በአባቶቻችን የህይወት መስዋትነት ተከፍሎበት ተጠብቆልን ይህው እኛ ልጆቻቸው እየተጠቀምንበት እንገኛልን።
ሆኖም ግን ሆን ብለው እኛን ለማሸማቀቅም እራሳችንን የበታች አድርገን እንድንጠላ እና የኔነው የምንለው ነገር እስክናጣ ድረስ ባገኙት አጋጣሚ ስለድህነታችን፣ረሃባችን፣ጎጠኝነታችን፣ሗላ ቀርነታችን፣ጦረኝነታችን ስለሚለፍፉት የረጅም እድሜ ቋንቋ ባለቤት መሆናችን እና አለም ላይ ላሉ ፊደሎች ሁሉ መነሻ አባት ፊደል እንዳለን ግን ለቀበሉት ቀርቶ ሲሰሙት እንኳን ኮሶ ጠጣ እንደተባለ ሰው ፊታቸውን ያጠቁሩታል እኛም ብንሆን ይህን የመሰለ የታሪክ ባለቤቶች ሆነን ሳለ የግድ ከባዕድ ጻህፍት እስኪነገረን ወይም እስኪጻፍልን ድረስ መጠበቅ የለብንም።
ሌላው ብከፍተኛ ሁኔታ አጽንዎት ሊሰጠው የሚገባ ነገር ልጆቻችን ይህንን ይመሰለ ለሌላም የተረፈ አባት ቋንቋ ባለቤት እና ተረካቢ መሆናቸውን ተረድተው ቋንቋቸውን እና ፊደላቸውን እንዲያውቁልን የተቻለንን ማድረግ ግድ ይለናል። ልጆቻችን በሰው ሀገር ሲኖሩ የራስ ቋንቋቸውን ባለማወቃቸው ማን እንደሆኑ ግራ እስቲገባቸው ድረስ እንዲሆኑ ተደርገዋል። የለም ኢትዩጵያዊ ነኝ እንዳይሉ ቋንቋውን፣ባህሉን፣በቅጡ አላወቁም እንዴትስ አድርገው እሴቶቻችንን ይረከቡን የለም ኢትዩጵያዊ አይደለንም እንዳይሉ "ኢትዩጵያዊ መልኩን ነብር ዥንጉርጉርነቱን አይለውጥም" የሚለው አምላካዊ ቃል በየሄዱበት የሚመለከታቸው ሁሉ ስማቸውን እንኳን ሳይጠይቅ ኢትዮጵያዊ ናችሁ እያለ ይጠይቃቸዋል ስለዚህ እነዚህ ተውልዶች ከየት ይሁኑ…? ታዲያ ለዚህ ምርጫ ለሌለው ጥያቄ መድሃኒቱ ልጆቻችንም ሆኑ እራሳችን የባህሪ ለውጥ በማምጣት እንከን ስለማይወጣለት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሐይማኖታችን፣ ስለቋንቋችን፣ፊደላችን እና ጨዋው ባህላችን መመለስ ይኖርብናል። ታዋቂው ኢትዮጵያዊ ባለቅኔ (ሎሬት) ጸጋዬ ገብረ መድህን ጦቢያ ምጽሄት ቅጽ 5 ቁጥር 11 1990 ዓ.ም. ገጽ 9 "አውሮፓውያን የ እስያ ቋንቋዎች (ግሪክ ላቲን ዕብራይስጥ ፅርዕ ዕረብ) እጀግ በጣም ብዙ የካም አበው ግሶችና ስሞች ዛሬም ተውርሰው የምናገኛችው። በኛ ባህል ላይ ተመሰርተው ነው ብስተኃላ የራሳችው ባህል የገነቡት። የፍልስፍናዎች ሁሉ መሪ ፍልስፍና ራስህን እውቅ ነው። እኛ ግን ዛሬ ሆዳችንን እንጂ ራሳችን አናውቅም" ሲሉ ጽፈዋል።
ታዲያ አብዛኞቻችን የባዕድ ቋንቋ ባለማወቃችን ሲያሽማቅቀን እና የበታችነት ስሜት ሲያላብሰን ይስተዋላል ይህ ግን አግባብ አይደለም የሰው ሀገር ቋንቋ አለማወቅ ሀጢያት አይደለም በጭራሽ ሊያሸማቅቀን አይገባም በርግጥ ቋንቋን ማወቅ ጠቃሚነቱ አጠያያቂ ባይሆንም የራስ ቋንቋን እያፈሩበት፣እያንቋሸሹ እና እያጣጣሉ መሆን በጭራሽ የለበትም።
ሲሆን ሲሆን ከ እግዚአብሄር የተሰጠን አለም ሁሉ ከኛ ፊደል በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ እየገለበጠ የሚጠቅምበት የፊልዶች አባት ቋንቋ ባለቤቶች የሆንን ቀና ብለን መሄድ እና ኮርተን ሌላውን ማስተማር ነበር የሚገባን።
ማጠቃለያ ታዲያ ይችህ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያናችን ከፈጣሪያችን ጋር የምታገኛኝን ብቻ ሳትሆን ጠቅላላ ማንነታችን ፣የታሪካችን፣ባህላችን፣ቋንቋችን እና የስልጣኔያችን መገኛ ምንጭ ናት። መንግስት ሆና ላለፉት ሺህ አመታት ሀገራችንን አስተዳድራለች ይህን ተከትሎ ስለ መንግስት አስትዳደር፣ ስለፍትህ እና ሰላም ይህ ነው የማይባል አስተዋጽዎ አድርጋለች ወደፊትም በሀገር ላይ መሰረታዊ እድገት እና ለውጥ ለማምጣት ተቋማቶች ቤተክርስቲያናችንን ምሰሶ አድርገው መነሳት ይኖርባቸዋል።ሌላው ክማንኛውም ሀገራችን ላይ ካለ የትምህርት ተቋም ፈርቀዳጅ በመሆን ብቻ ሳይሆን የትምህርት ሚኒስቴርም በመሆን እስከ ቅርብ ግዜ ድረስ አገልግላለች።
ለዚህ ነው በዚህ ውጥንቅጡ በወጣ አለም ልጆቻቸውን ይዘው ወደ እግዚአብሄር ቤት ሲመጡ ስለ ሀይማኖታችው ብቻ ሳይሆን ስለቋንቋችው፣ሀገራቸው፣ ቅርሳቸው፣ ባህላቸው በጠቅላላ ስለ ማንነታቸው በይበልጥ እንዲያውቁ ይረዳቸዋል።
ማንነታቸውን በሚገባ የተርዱ እና ያወቁ ብሎም ሌላውን ማንነቱን እንዲያውቅ እና እንዲረዳ ይህንን ቤተክርስቲያኖችን በማቋቋም ጀምሮ በመምራት በማስተዳደር የቦርድ አባል በመሆን በማገልገል ተሳታፊ በመሆን ሌላው ወደ ቤተክርስቲያን እንዲመጣ የሚቀሰቅሱ ሁሉ በጠቅላላ የሚቀጥለው ትውልድ ማንነቱን እንዲያውቅ ጥረት የሚያድርጉ ስለሆነ እግዚአብሄር የድካማችውን ዋጋ በእጥፍ እንዲከፍላቸው እና የመንግስቱ ወራሽ ያድርጋቸው በማለት እስናበታለሁ።
ስብሃት ለእግዚአብሄር