አይሮፕላን መጣ እየገሰገሰ
በዘፈን እንደኛ ጥላሁን ገሠሠ
እሁድ ሚያዝያ 19,2009 የፋሲጋን በአል ኒውዮርክ እና ኒውጀርሲ ከቤተስቦቼ ጋር በጥሩ ሁኔታ አሳልፌ ወደ ሜሪላንድ ስለመጣሁ ሰኞ እለት ስራ የገባሁት የሞት ሞቴን ነው ሰኞ እና ሰኔ የሚያስብል ቀን ነበር ክረምቱ ወጥቶ በጋ መግቢያው ሰአት ላይ ስለሆነ ሰማዩ ልዝነብ እልዝነብ የሚል ጭቅጭቅ የያዘ ይመስላል መቼም አይደርስ የለ ከስራ መውጪያዬ ሰአት ደረሰ ያጋጣሚ ነገር ሆኖ በመስሪያ ቤቱ የምሽት ፈረቃ የሚሰራው አማርኛ ተናጋሪ ስለነበር እንደ ተለመደው ሰላምታ ከተለዋወጥን በሃላ "ሰማህ ጥላሁን ገሠሠ መሞቱን" አለኝ እኔ ደግሞ የቱ ጥላሁን ስለው "ሌላ ጥላሁን የለ ጥላሁን ገሠሠ ነዋ!!!" ወዲያውኑ ኬኔትኬት የምትኖር እህቴ ደውላ የጥላሁንን መሞት አረጋገጠችልኝ ከዛ በሃላ ቤቴ እስክደርስ ድረስ ከተለያየ ሰው ሰማሁ።
ሁላችንም ብንሆን በጥላሁን ዘፈን ይብዛም ይነስ ትዝታዎች አሉን በአብዛኞቻችን እድሜ ክልል ውስጥ ዘፈኖቹ አልፈዋል በተለይ ሙሽራዬ እና ሃይ ሎጋ ሲባል የጥላሁን የህይወቴ ህይወት የማይቀር ዘፈን ነው ሙሽራው እና ሙሽሪት ተቃቅፈው ሲያበቁ በጥላሁን ዘፈን "የህይወቴ ህይወት አንቺ በመሆንሽ እባክሽ ፍቅሬ ሆይ አልጥፋ ከፊትሽ" እያሉ ሲያዜሙ የኔስ መቼ ነው ያስብላሉ።በበኩሌ ሁሉንም የጥላሁን ዘፈን እወዳለሁ ማለት አይደለም ለምሳሌ "ዋይ ዋይ ሲሉ" የሚለውን ዘፈን በጣም ነው የምጠላው 1984 ዓ.ም. የ6ኛ ክፍል ተማሪ እያለሁ በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች እርዳታ እና ገቢ ማሰባሰቢያ በሰፊው ይካሄድ ነበር የዘፈኑ ማጀቢያ በ 1977 ዓ.ም. በድርቅ የተጎዱ ወገኖች ቪዲዬ ነበር ታዲያ በዚህ የዘፈን ቅንብር ላይ በድርቅ ህይወታችውን ያጡ ህጻናት በጅምላ መቃብር ሲቀበሩ እና ምግብ ሲታደል ያለውን ሽሚያ የሚያሳይ ነበር። ከዛ ወዲህ ይህንን ዘፈን ቁጭ ብዬ ልሰማው ቀርቶ ያጋጣሚ የሆነ ቦታ እንኳን ተከፍቶ ስሰማ የምገባበት ነው የሚጠፋኝ።
ጥላሁን በአማካኝ ከ400 በላይ ዘፈኖችን ለሶስት ትውልዶች ተጫውቷል ይባላል። ምክንያቱን ባላውቅም ህዝብ ለህዝብ የተጫወተው "ወደፊት በሉለት ይለልይልት" የሚለው ደስይለኛል በተረፈ ዘፈኖቹ አቃቂር የሚወጣላችው አይደሉም። ከኦሮምኛ ደግም "ሰላማካ ያደሜ ሰላማካ" ሰምቼ አልጠግባችውም።
ለመጀመርያ ጊዜ ጥላሁንን በቅርበት የትመለከትኩት አዲስ አበባ በ1998 አ.ም. ሳር ቤት አካባቢ የሚገኘው ካልዲስ ካፍቴሪያ ውስጥ ነው። የምሰራው እዛው ህንጻ ላይ ስለሆነ ቡና እና ሻይ ለማለት አይርቀኝም የዛን እለት ልክ እንደዛሬው ቀኑ ዝናባማ ስለነበር ቡና ልበል ብዬ ወደ ካልዲስ ጠጋ ስል ጥላሁንን አየሁት ሰዎች ፊርማውን እንዲፈርምላችው በመኪናው መስኮት በኩል ሲረባረቡ ተመለክትኩኝ አይ ቡናዬን ልግዛና ሰው ትንሽ ገለል ሲል አናግረዋለው አልኩኝ ታዲያ ቡናዬን ይዤ ስመለስ ሰው የለም ጠጋ ብዬ ስጠይቅ አይ ጥላሁን ጨርሶ ሊሄድ ነው አሉኝ ያለበት መኪና መስኮት ተዝግቶ አይስክሬሙን በማንኪያ ሲያጣጥም አየሁት ለሁለተኛ ጊዜ እና ለመጨረሻ ጊዜ ያየሁት በዋሽንግተን ዲሲ የኢትዮጵያ ስፖርት ፌደሬሽን በሰሜን አሜሪካ የብር እዩቤልዩ በሚከበርበት ጊዜ በግላጭ ተገናኘና በዊልቸር በሴት ልጁ እየተገፋ ህዝቡን ሰላምታ ሲሰጥ ነበር ያጋጣሚ ሆኖ በግላጭ ስላገኝሁት ጠጋ በማለት ጉልበቱን እና ሁለቱንም እጆች አይበሉባ ስሜ ሳበቃ ጋሽ ጥላሁን እንኳን አደረሰህ አልኩት እሱም "እግዚአብሔር ያክብርልን የኢትዩጵያ አምላክ ይጠብቃችሁ" አለ። በመቀጠልም ለማስታዎሻ አብረን ፎቶ ተነሳን ፊቱ ኮስታራ ነው ፈገግ ሲል እንኳን አላየሁትም ግርማ ሞገስ አለው ቁጭ ብሎ እንኳን ረጅም መሆኑ ያስታውቃል። በአንድ በኩል በጣም እድለኛ ነኝ ጥላሁን ገሠሠ ላይ መድረሴ ምናልባት ከዚህ በሃላ እንደሚመጣው ትውልድ ጥላሁንን በነበር ከሚያውቁት ጋር መመደብ አይቀርልኝም ነበር። የጥላሁን ገሠሠ ድንገተኛ አሟሟት አሰደንጋጭ በመሆኑ ዜናው የተለያዩ የብዙሃን መገናናን አርዕስተ ዜና ሆኖ ነበር ያለፈው ቀብር ስነ-ስርዓቱ በተፈጸመ በሳምንቱ ዋሽንግተን ዲሲ በሚገኘው ማርያም ቤትክርስቲያን ላይ በተደረገው የፍትሃት ስነስርአት ላይ ተገኝቼ ነበር።ጥላሁን ገሠሠ በህይወት ባኖርም በሙዚቃዎቹ ሲታወስ ይኖራል። እግዚአብሄን ነፍሱን ይማረው ለቤተሰቡም መጽናናትን ይስጣችው።
No comments:
Post a Comment